የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የአማራ ክልል መንግስት በወሎ ኦሮሞዎች ላይ እያካሄደ ያለውን የተቀናጀ ጦርነት በድጋሚ በጽኑ ያወግዛል።
በወሎ ኦሮሞዎች ላይ በተከፈተ የተቀናጀ ጦርነት የህዝብ ህይወት እየተቀጠፈ እን ንብረት እየወደመ መሆኑን ኣስመልክቶ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ርዕሰ አንቀጽ – ጥር 24 ቀን 2023ዓም
በሰሜን ኦሮሚያ የአማራ ክልል መንግስት በኦሮሞ ህዝብ ላይ በከፈተው የተቀናጀ ጦርነት የሰላማዊ ዜጎች ህይወት እየጠፋ ይገኛል። የወሎ ኦሮሞዎች ቤትና ንብረት እየወደመና እየተዘረፈ ነው።
የወሎ ኦሮሞዎች በኣስተዳደር ከኦሮሚያ ተቆርጠው በአማራ ክልል ስር እንዲተዳደሩ እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል። በተለያዩ ጊዜያት በአማራ ክልል እና በፌዴራል መንግስት ሃይሎች የተደራጁ እኩይ ዘመቻዎች በህዝቡ ላይ የህይወትና የንብረት ውድመት ሲያስከትል ነበር። ይህ ወረራ እስካሁንም ሳይገታ ወይም መፍትሄ ሳያገኝ ዛሬን ደርሷል። አሁንም ይኸው ተመሳሳይ ሁኔታ ነው በወሎ ኦሮሞዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው።
እ.ኤ.አ. ጥር 21 ቀን 2023ዓም በሰሜን ኦሮሚያ ወሎ ዞን ጂሌ-ዱሙጋ ወረዳ ውስጥ የአማራ ልዩ ሃይል የኦሮሞ ኣርሶ ኣደሮችን በከባድ የጦር መሳሪያ በማጥቃት በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል፣ የነዋሪውን ቤትና ንብረትም ኣውድሟል። ይህ ጦርነት በአማራ ልዩ ሃይል እና ፋኖ በተባለው አሸባሪ ቡድን የተቀናጀ መልኩ እየተካሄደ ሲሆን፡ ጦርነቱን አቀናጅቶ ህዝብ በማስፈጀት ላይ የሚገኘው የአማራ ክልል መንግስት ነው። ከአማራ ክልላዊ መንግስት እውቅና ውጪ በወሎ ውስጥ እየሆነ ያለ ነገር የለም።
የአማራ ክልላዊ መንግስት የአማራ ክልል ልዩ ሃይል፣ ፋኖ እና የአማራ ሚሊሻ እንዲሁም የከሚሴ ዞን ወረዳ ካቢኔዎችን በኣስተባብርና በማቀናጀት የኦሮሞ አርሶ አደሮችን በመውጋት ላይ ይገኛል። የፌደራል መንግስት መዋቅሮች የአማራን ታጣቂዎች በድብቅ ከመርዳት በስተቀር የወሎ ኦሮሞ ህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አንዳችም ጥረት ኣድርገው ኣያውቁም። ይልቁንም የአማራ ክልል መንግስትን በመርዳት በተለያዩ ጊዜያት የወሎን ህዝብ እያስፈጀ ያለው የፌደራል መንግስት መሆኑ ይታወቃል።
የፌደራል መንግስት የጸጥታ መዋቅር ባለበት ይህ ህዝብ በተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶበት በጅምላ ስለመገደሉ፣ ቤት-ንብረቱ ስለመውደሙ ብዙ መረጃዎች ማረብ ይቻላል። ይህም የፌደራል መንግስት የዚህን ህዝብ ደህንነት እየጠበቀ እንዳልሆነ ያመለክታል። ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው።
ባለፉት 3 ቀናት ከ65 በላይ የወሎ ኦሮሞ አርሶ አደሮች በቀዬኣቸው ተገድለዋል። በትላንትናው ዕለት፡ ጥር 23 ቀን 2023ዓም ብቻ ስማቸው ያልታወቁ 39 ሰዎች በነዚሁ የአማራ ክልል መንግስት ታጣቂዎች ተገድለዋል። በርካቶችም በጥይት ተመተው የቆሰሉ ሲሆን ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል። በርካታ የህዝቡ ቤቶችም ከነንብረታቸው ተቃጥለዋል።
እ.ኤ.አ. ጥር 23 ቀን 2023ዓም ከፊንፊኔ ወደዚያ ሲጓዙ የነበሩ የወሎ ኦሮሞዎች ሸዋ ሮቢት አካባቢ ካረ-ጀጀባ በተባለ ቦታ የመታወቂያ ወረቀታቸው ታይቶ በመለየት ከተሽከርካሪ ላይ እንዲወርዱ ተደርገው 16 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ጦርነቱ አሁን ወቅት በጂሌ-ዱሙጋ ወረዳ ውስጥ ወደ ሚገኙ የገጠር መንደሮች እና ከተሞች እየተዛመተ ነው። በወሰን ቁርቁር፣ ኮላሽ፣ አላላ ድሪጭ፣ ኩንዴ፣ ዋጩ፣ ባልጪ፣ ወለኮ እና ጎዳ ቀበሌዎች እንዲሁም አጣዬ እና እና ሰምበቴ ከተሞች በተካሄደው ጦርነት የበርካታ ሰዎች ህይወት መቀጠፉና ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በወረራው ጦርነት ከመቶ በላይ ዜጎች የቆሰሉ ሲሆን የህዝቡ ቤቶችና ንብረትም እንዲወድም ምክንያት ሆኗል። የጤና ተቋማት በአማራ ክልል መንግስት ቁጥጥር ስር በመሆናቸው በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ህክምና ተነፍገው እየሞቱ ነው።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የአማራ ክልል ታጥቂዎች እና ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች በወሎ ኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያደረሱትን ህገ-ወጥ ወረራና እና የጅምላ ግድያ እንደካሁን ቀደሙ በጽኑ እያወገዘ፡ ከዚህ አረመኔያዊ እና እኩይ ድርጊታቸው እንዲገቱ ይጠይቃል። ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ የገደሉ ሰዎች በህግ ፊት ሊጠየቁ ይገባል የሚለውም የኦነግ አቋም ነው።
የኦሮሞ ህዝብ ይህን በተስፋፊ የመሬት ወራሪዎች በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመመከት ከያለበት ሁሉ ለወሎ ኦሮሞዎች መድረግ ኣለበት። በተለይም ጦርነቱ እየተካሄደ ባለበት አካባቢ ኣቅራቢያ የሚገኙ የወሎ ኦሮሞዎች በመረጋዳዳት ወረራው ለተፈጸመበት ወገናቸው መድረስና መረዳዳት ወሳኝ ነው። መላው የኦሮሞ ህዝብ በቀዬው ላይ ሊያጠቁት የሚመጡትን ማናቸውንም ሃይሎች ሁሉ ለመመከት ዘወትር እራሱን ማዘጋጀት አለበት።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የአማራ ክልል መንግስት በወሎ ኦሮሞዎች ላይ እያካሄደ ያለውን የተቀናጀ ጦርነት በድጋሚ በጽኑ ያወግዛል።
ድል ለሰፊው ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ጥር 24 ቀን 2023ዓም
ፊንፊኔ፡ ኦሮሚያ


Sagalee Bilisummaa Oromoo












Leave a Comment
Your email address will not be published. Required fields are marked with *