መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ጥቃት እያወገዝን፣ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድና ተጨማሪ ግድያዎችን እንዲያቆም እንማጸናለን።
አለምአቀፍ የኦሮሞ የህግ ባለሙያዎች ማህበር በምዕራብ ኦሮሚያ በሰው-ኣልባ ኣውሮፕላን(ድሮን) በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቆ ያወግዛል።
አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2018 ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በኦሮሚያ ምዕራብና ደቡብ አካባቢዎች ንፁሀን ዜጎችን ያለ አግባብ እየገደለ ነው። በምእራብ ኦሮሚያ ጥቃቱን አጠናክሮ በመቀጠል፣ በሰው-ኣልባ ኣውሮፕላን(ድሮን) እና በተዋጊ ጀቶች በፈጸመው የኣየር ላይ የቦምብ ድብደባ ጥቃቶች በትምህርት ቤቶችና በገበያ ቦታዎች ህጻናትና አዛውንቶችን ያካተቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል።
በቅርቡም መንግስት በምዕራብ ኦሮሚያ በሰው-አልባ አውሮፕላኖችን በርካታ ጥቃቶችን ፈጽሟል። ጥቅምት 19 እና ጥቅምት 23 ቀን 2022ዓም በሰው-አልባ አውሮፕላኖች በምዕራብ ሸዋ ጮቢ ወረዳ በሜታ ወልቂጤ ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ንፁሃን ዜጎችን ተገድለዋል። እ.ኤ.አ. በህዳር 2 ቀን 2022ዓም መንግስት በርካታ ሰው-አልባ አውሮፕላኖችን በአካባቢው ካሰማራ በኋላ ህፃናትን፣ ተማሪዎችንና አዛውንቶችን ያሉበት በርካታ ንፁሀን ዜጎችን ጨፈጨፈ። እ.ኤ.አ. ህዳር 9 ቀን 2022ዓም መንግስት በመንዲ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሌላ ሰው-አልባ የቦምብ ጥቃቶችን በመፈጸም በርካታ ሲቪሎችን በመግደል በመቶዎች የሚቆጠሩትን አቁስሏል። አለምአቀፍ የኦሮሞ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ለዚህ ኣሰቃቂ የመንግስት ጥቃትም የአይን እማኞች፣ ምስሎችና የጥቃቱ ድርጊቶችን የሚያሳዩ የቪዲዮ ቅጂዎችን እንደማስረጃ ይዟል።
መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ጥቃት እያወገዝን፣ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድና ተጨማሪ ግድያዎችን እንዲያቆም እንማጸናለን። ወንጀለኞቹ የኢትዮጵያ መንግስት የስምምነቱ አካል የሆነበትን ኣለምኣቀፉን የጄኔቫ ስምምነትን በመጣስ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል በመፈፀማቸው ሊጠየቁ ይገባል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የሮም የአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ህግ አካል ባትሆንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ለኣለምኣቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት እንዲመራው እንጠይቃለን።
በጣም የሚገርመው ጸረ-ቶርቹር፣ ማሰቃየትና ሌሎች ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰብአዊ አዋራጅ አያያዝን ጨምሮ ኢትዮጵያ የበርካታ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አካል ነች። እነዚህ ስምምነቶች መንግስት ለሲቪሎች ጥበቃና ዋስትና እንዲሰጥ ያሳስባሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለራሱ ህገ-መንግስትና ህጎች ክብር በማይሰጥበት ሁኔታ የኣለምኣቀፍ ውሎችና የስምምነቶችን ያከብራል ብለን አንጠብቅም።
አለምአቀፍ የኦሮሞ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት የንፁሃን ዜጎችን ግድያ እንዲያቆም ጫና እንዲያደርግ ይማጸናል። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያ የተፈፀመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያጣራም እንጠይቃለን።
አለምአቀፍ የኦሮሞ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የስራ-ኣስፈጻሚ ቦርድ
ግልባጭ፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ቢሮ
የአውሮፓ ህብረት,
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣
ሂዩማን ራይትስ ዎች

Sagalee Bilisummaa Oromoo












Leave a Comment
Your email address will not be published. Required fields are marked with *